የዐማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች

አራተኛ እትም

© በፋኖ ዘሳይበር የትዊተር የውይይት ክበብ የተሰባሰበ።
መጋቢት ፳፻፲፮| March 2024

መቅድም

  • ነጻ ሕዝብ እና ነጻ አእምሮ ከመጠየቅ አይቦዝንም፤ ለጥያቄውም መልስ ይሻል። የዐማራ ሕዝብም ላለፉት አስርታት አመታት፤ ምንም እንኳን መልስ ባያገኝም ከመጠየቅ እና ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ በሰለጠነ መንገድ ከመሟገት አልቦዘነም። የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመነጩት፤ ታሪካዊ ጠላቶቹ ካደረሱበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤ ባህላዊ፣ የዘር ማጥፋት፣ ወዘተርፈ በደሎች እና ፀረ-ዐማራ ትርክቶች ነው። እነዚህን በደሎች ለመመከት እና እንደ ህዝብ ቀጣይነቱን እና ዘላቂ ደኅንነቱን ለማስጠበቅ እንዲችልም በጠራ የትግል አቅጣጫ መመራቱ የግድ ይሆናል። የትግል አቅጣጫ ጥራትን አስፈላጊነት ከሚያስረግጡ ማመላከቻዎች መካከል ባለፉት ሃምሳ (50) ዓመታት የነበሩ የታሪክ እጥፋቶች ዋቢ ናቸዉ። የዐማራ ሕዝብ በተደጋጋሚ፤ ልጆቹ በመስዋዕትነታቸው ለውጥ አምጥተው ሌሎችን ካነገሱ በኋላ ባነገሷቸው አካላት ተክዶ፣ ታግሎ ካስወገደው ሥርዓት በባሰ አገዛዝ ስር ሲወድቅ ኖሮ በስተመጨረሻም አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ የኅልዉና አደጋ ተጋልጦ በሞት ሽረት ትግል ውስጥ ይገኛል።
  • በዚህ ሰነድ መንፈስ፤ የኅልውና አደጋ ሲባል፤ ሆን ተብሎ ትርክት ተፈብርኮለት፣ አቀንቃኝ እና ደጋፊ ጀሌ ተፈጥሮለት፤ ሥርዓትም ተመሥርቶለት ዐማራውን በአካል፣ በኤኮኖሚ፣ በዕሴት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በአሰፋፈር፣ በቅስም፣ እንዲሁም የሱ በሆኑ እና ባልተዘረዘሩ ነገሮች ማዳከም እና ቢቻል ዝርው አድርጎ መበተንን እና ማጥፋትን ያለመ የተቀናጀ ጥቃት ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። በአጭሩ፤ ዐማራን እና ዐማራነትን ከምድረ ገጽ የማጥፋት እሳቤ ግዘፍ ነስቶ መንግሥታዊ ሥርዓት መሆኑ ነው።
  • ከላይ የተጠቀሱት ተከታታይ የለውጥ ክሽፈቶች የደረሱት በከፊል፤ ዐማራ ተደራጅቶ ታማኝ እና ጽኑ አቋም ባላቸው መሪዎች ባለመመራቱ እና ከዚህም የተነሳ የጠራ፣ የተሰነደ፣ እና በቀላሉ የሚታወስ የመታገያ ጥያቄዎች ዝርዝር እና በግልጽ የቀረቡ የመታገያ አማራጮች ባለመኖራቸው ነው።
  • በመሆኑም፤ ነባሮቹን ጥያቄዎች ካሁን በፊት በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ተመርኩዞ፤ በቅርቡ ደግሞ በተካሄዱበት ተደጋጋሚ የትህነግ ወረራዎች እና አሁን በአክራሪው የኦሮሞ ኃይል አጋፋሪነት እየተካሄደ ባለው፡ በጦር ሠራዊት የታገዘ የዘር ማጥፋት ተግባር ምክንያት የመጡ አዳዲስ ጥያቄዎችን በመጨመር እንዲሁም በዐማራዉ የኅልዉና ትግል ውስጥ አስተዋጽዖ በሚያበረክቱ ንቁ አማራዎች ልምድ እና ዕይታ በማዳበር “የዐማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች” የውይይቱ የማጠቃለያ ሰነድ ሆኖ ተዘጋጅቷል።
  • ማንም እርግጠኛ ሊሆንበት የሚገባው ሐቅ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የመነጩት፤ እኩልነትን፣ ፍትሕን፣ ሰላምን እና ዘላቂ ደህንነትን ከመሻት እንጂ፤ ማንንም ማኅበረሰብ ከመጥላት ወይም ለመጉዳት ከማለም አለመሆኑ ነው።
ድል ለዐማራ ሕዝብ!

 

የዐማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በዝርዝር
  1. በዐማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን የኅልዉና አደጋ ማስወገድ
    1. የዐማራ ሕዝብን ጅምላ ጭፍጨፋ ጨምሮ የተጋረጡ የህልዉና አደጋዎችን በአስተማማኝነት እና በዘላቂነት መቀልበስ፤
  2. ሰላም እና ፍትሕ ማስፈን
    1. በዐማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ ድርጅቶች (ትህነግ፣ ኦነግ (የተለያዩ ቅርንጫፎቹን ጨምሮ)፣ ብልጽግና እና ሌሎች)፣ የድርጅት መሪዎች፣ በተለያየ የሥልጣን እርከን የተሳተፉ፣ የዘር ፍጅት እንዲፈጸም ሰነድ ያዘጋጁ፣ ጥቃት ያቀዱ፣ ያነሳሱ ወይም ያስተባበሩ እና የዘር ፍጅት የፈጸሙ ግለሰቦችን ለፍርድ ማቅረብ፤
    2. የዘር ፍጅት እንዲፈጸም አስተዋጽዖ ያደረጉ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በክፋት የታሪክ መዝገብ እንዲሰፍሩ፣ እንዲሁም ምልክቶቻቸው በሕግ እንዲታገዱ፤ ለተፈፀሙ ግፎች ማስታወሻ አና ማስተማሪያ የሚሆኑ ምልክቶች እንዲቆሙለት እንዲሁም በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካቶ ትውልድ እንዲማረዉ እንዲደረግ፤
    3. ዐማራነታቸው እንደ ጥፋት ተቆጥሮ በሀገሪቱ በሚገኙ በግልጽ በሚታወቁ እና በማይታወቁ እስር ቤቶች በመንገላታት ላይ የሚገኙ ንጹሓን ዐማራዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤ እንዲሁም እነሱ እና ካሁን በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ካለጥፋታቸው ታስረው የተንገላቱ ዐማራዎች ፍትሓዊ ካሳ እንዲከፈላቸው፤ በማሠር እና በማሰቃየት ወንጀል የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ፤
    4. የዐማራ ሕዝብ በማንነቱ ምክንያት መገደል፣ መሰወር፣ መሳደድ እና በሰላም ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ አለመቻል በአስተማማኝ እና በዘላቂነት እንዲቆም፤
    5. በዐማራ ማንነታቸው ምክንያት የተፈናቀሉ ወደነበረ ይዞታቸው ወይም ወደ ምትክ ይዞታ ተመልሰው እንዲቋቋሙ፣ ለወደመ ንብረታቸውም ፍትሓዊ ካሳ ለራሳቸው ወይም ለቅርብ ዘመዶቻቸው ወይም ለቤተሰቦቻቸው አንዲከፈላቸው፤
    6. በመላ ሀገሪቱ ለሚገኘዉ የዐማራ ህዝብ በማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ጭቆና፣ እስር፣ እንግልት እና የተዛባ ፍርድ /መድልዎ እንዲያከትም፤
    7. በተለያዩ ጊዜያት የተሰወሩ ዐማሮች ዕጣ ፈንታቸው ተጣርቶ፤ በሕይወት ካሉ ከቤተሰቦቻቸው እንዲገናኙ፤ በሕይወት ከሌሉም ቤተሰቦቻቸው በአግባቡ እንዲረዱ እና ፍትሓዊ ካሳ እንዲያገኙ፣ ወንጀለኞችም ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ፤
    8. የዐማራን እምነት ትከተላላችሁ፣ ከዐማራ ጋር ትዛመዳላችሁ፣ ለዐማራዉ ትቆረቆራላችሁ፣ የዐማራ ቋንቋ ትናገራላችሁ ወይም በአጠቃላይ የዐማራ እሴት ተላብሳችኋል በሚል ምክንያት ለተገደሉ ወይም የአካል እና የሞራል ጉዳት ለደረሰባቸዉ ዐማራዎች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው ወይም ለቅርብ ዘመዶቻቸው ፍትሓዊ ካሳ እና ይዞታ እንዲሰጣቸው፤
    9. በተደጋጋሚ በዐማራ ሕዝብ ላይ ለተደረጉት ሕገ ወጥ ወታደራዊ ዘመቻዎች እና በዘመቻዎቹ ለጠፋዉ የሰው ሕይወት፣ ንብረት፣ እንዲሁም በዚያ ምክንያት ለተጎዳዉ ኤኮኖሚ፣ ለተስተጓጎሉ የትምህርት አና የጤና አገልግሎቶች፣ በነዚህም ምክንያት ለመከኑ ዕድሎች (opportunity costs) እና የነዚህን ዕድሎች የረጂም ጊዜ “ወለድ” መነጠቅ የዳረጉ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ሕዝቡ እንዲካስ እና ተጎጂ ቤተሰቦችም ካሳ እንዲከፈላቸዉ፤
    10. የዐማራ ሕዝብ ከመሠረታት እና በዋናነት ከገነባት መዲና፣ ከአዲስ አበባ በግፍ የተፈናቀሉ በሙሉ ወደቦታቸዉ እንዲመለሱ፣ ካሳ እንዲከፈላቸዉ እንዲሁም ተመጣጣኝ የፖለቲካ ሥልጣን ውክልና እና ፍትሐዊ የኤኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲያገኙ፤
  3. የህገ መንግሥት መሻሻል እና ፖለቲካዊ ውክልናን ማረጋገጥ
    1. የዐማራ ሕዝብ በተዓማኒ ሂደት በመረጣቸው ወኪሎቹ ሙሉ ተሳትፎ፤ ህገ መንግሥቱ እና ሌሎች ዐማራን ያገለሉ ወይም የሚጎዱ ህጎች እና አሠራሮች እንዲለወጡ/ እንዲሻሻሉ፤
    2. ከዐማራ እና ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተወለዱ የኢትዮጵያ ዜጎችን፤ ከሌሎች እኩል የሀገር ባለቤት የሚያደርግ፤ እንዲሁም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚያረጋግጥ ህገ መንግሥት እንዲቀረጽ፤
  4. ትክክለኛ የሆነ የህዝብ ቆጠራ ማካሄድ
    1. በመላይቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ ዐማራዎች እና የዐማራ ተወላጆች ትክክለኛ ቁጥራቸዉ፤ እንዲሁም ተዓማኒ የሕዝብ ስርጭት እና ስብጥር ይፋ እንዲደረግ፤
    2. የዐማራ ሕዝብ ቁጥር ሆን ተብሎ በመቀነሱ ምክንያት ለተነጠቀው የበጀት መጠን ማካካሻ እንዲከፈለው እንዲሁም ለደረሰው የ”ወለድ” መነሳት ካሳ እንዲከፈለው፤
  5. ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነትን ማስፈን
    1. የዐማራ ሕዝብ፤ ቁጥሩን፣ ለመንግሥት የሚከፍለዉን የግብር መጠን እና ምርታማነቱን ያገናዘበ የልማት ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ፤
    2. ክልሉ ሰፊ ሰብል አምራች ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የተሻለ ምርታማነትን የሚያሳድግ የግብርና ቴክኖሎጂ በፍትኃዊነት እንዲቀርብለት፤
    3. የቱሪስት ጸጋዎቹን ባገናዘበ መልክ፤ ከቱሪስቶች የሚሰበሰብ ገቢ በፍትኃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆን፤ ጸጋዎቹም እንዲጠበቁለት፤
    4. አስተማማኝ የሆነ የባለሀብቶች፤ የአልሚዎች እና የነጋዴዎች ንብረቶች ጥበቃ እንዲደረግ፤
    5. የዐማራ ሕዝብ ለደረሰበት የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የሌሎች አገልግሎቶች እና የልማት መሠረቶች ፍትሓዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጡለት፤ እስካሁን ለደረሰውም የ”ወለድ” መነሳት ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፈለው፤
  6. ፀረ-ዐማራ ትርክቶችን ማረም
    1. በምርምር ያልተረጋገጡ እና በቂ ማስረጃ የሌላቸውን “ታሪኮች” እንዲሰረዙ፣ ትክክለኛው ታሪክ በወጥነት ለታሪክ ትምህርት ግብአት እንዲደረግ።
    2. የፈጠራ “ታሪኮች“ን ለፖለቲካዊ ተግባር ማካሄጃነት ማዋል በሕግ እንዲታገድ፤
    3. በፀረ ዐማራ ትርክቶች ምክንያት ለጠፋው ሕይወት፣ ንብረት እና ለተስጓጎለው ማኅበረሰባዊ ዕድገት ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፤ ተበዳዮች ወይም ወራሾቻቸውም እንዲካሱ፤
    4. የፀረ ዐማራ “ታሪኮች” ምልክቶች በሕግ እንዲታገዱ ያሉትም እንዲወገዱ፤
    5. በቅርሶች ላይ የሚደረጉ የማንነት ቅየራ፣ የማፍረስ እና ሌሎች የማጥፋት ተግባራት እንዲቆሙ፤ ለዘላቂውም እንዲቀለበሱ እና ቋሚ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፤
  7. የማንነት፣ የባለቤትነት እና የአስተዳደር ወሰን መብቶችን ማረጋገጥ
    1. በገዢዎች ያለበቂ የታሪክ፣ የአሰፋፈር ወይም የማንነት መስፈርት በኃይል ከዐማራዉ የተወሰዱ እና ወደ ሌሎች የተካለሉ የዐማራ ርስቶች፣ ንብረቶች፣ የቦታ ስያሜዎች፣ ባህሎች እና የማንነት ጥያቄዎች እንዲመለሱ፤
    2. ወልቃይት፣ ራያ፣ ሸዋ፣ መተከል፣ ቢዛሞ፣ እና የዐማራ ሕዝብ በብዛት የሚኖርባቸው/ወይም ይኖርባቸው የነበረ ከተሞች እና ሌሎች ዐማራው በግፍ የተነጠቃቸው እና የተሳደደባቸው ታሪካዊ ግዛቶች ለተነጠቀው ነባር ሕዝብ እንዲመለሱለት፤
    3. በኃይል እና በወረራ የተቀየሩ የቦታ ስያሜዎች እና ባለቤትነቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ፤ ለቀደምት ባለቤቶችም ዕውቅና እንዲሰጥ፤
  8. ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ የውርስ እና የቋንቋ መብቶችን ማረጋገጥ
    1. የባህል እና የቅርስ ውርሶች ጥበቃ እና በነሱ የመገለጥ መብት እንዲረጋገጥ፤
    2. የኃይማኖት ተቋማት ነጻነታቸው እና ውርሶቻቸው እንዲከበሩ፤
    3. የዐማራ ሕዝብ ልጆች በቋንቋቸው እና የአያት ቅድማያት ውርስ በሆነው ስርአተ ፊደል የመጠቀም መብታቸው ካለምንም ገደብ እንዲከበር፤ ራሱ ሕዝቡ በሚከፍለው ግብር ልጆቹ ሌሎች ቋንቋዎች እና ሀሰተኛ ትርክቶች በግድ አንዲማሩ ማስገደድ እንዲቆም፤
    4. የዐማራውን መልካም አስተዋጽዖ የሚገልጹ ምልክቶች እንዲስፋፉ እና እንዲተዋወቁ፤
  9. ስር ነቀል የሥርዓት ለውጥ፣ ፍትሕን እና ራስን የማስተዳደር መብትን ማረጋገጥ
    1. ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች በተደጋጋሚ የዐማራ ሕዝብ እና ሌሎች የዜግነት መብታቸውን የተነጠቁ የኢትዮጵያ ዜጎች በሰለጠነ መንገድ ለረጂም ጊዜ ሲጠይቁ የቆዩ ቢሆንም አገዛዙ ለመመለስ ባለመፍቀዱ እና ይባስ ብሎም ፍትሓዊ ጥያቄ ባነሳው የዐማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት በመክፈቱ እና በሰላማዊ መንገድ ሊቀለበስ የማይችል የኅልውና አደጋ በመጋረጡ፤ ከላይ የተነሱትን ፍትሓዊ የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሙሉ ለማስመለስ ስር ነቀል የሥርዓት ለውጥ አማራጭ የሌለው ጥያቄ ሆኗል!
    2. ከስር ነቀል የሥርዓት ለውጥ በኋላ፤ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አና ማኅበረሰባዊ መስተጋብር፣ የዐማራ ሕዝብን ጥያቄዎች እና ፍትሓዊ የሥልጣን ድርሻዎች ያማከለ ሀገር አቀፍ ውይይት እና የሽግግር መንግሥት ምሥረታ።
    3. ፍትሓዊ የሥልጣን ድርሻውን ይዞ፤ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ፍትሕ ያሰፈነች፣ ሁሉንም ዜጎቿን በእኩልነት የምታይ እና የዐማራ ሕዝብን ዘላቂ ጥቅም የምታከብር ሀገር መመሥረት፤ ያ ካልተቻለ ግን የዐማራ ሕዝብን አጠቃላይ ፍትህ እና የድርሻ ጥያቄዎች ያከበረ መለያየት መፈጸም።

 

ለአስተያየቶች፤

በትዊተር፤ ፋኖ ዘሳይበር (@fano_z_cyber)

በኢሜይል፤ ataskforce6@gmail.com

Flyer-color-600px-1

የዐማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በበራሪ ወረቀት መልክ

Flyer-color-600px-1

Basic Amhara Demands as a flyer

Flyer-color-600px-1

የዐማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በኪነጥበብ (ቅምሻ)

Flyer-color-600px-1

የዐማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በኪነጥበብ (X-space)

Flyer-color-600px-1

የ"ጥያቄዎችችን" ሙዚቃ (ሆ! እያለ...) በቪድዮ

Flyer-color-600px-1

የዐማራ ሕዝብ የኅልውና አደጋዎች ምንድን ናቸው?