የኅልውና አደጋ ማለት ምንድን ነው?

የኅልውና አደጋ ማለት ምንድን ነው?
በፋኖ ዘሳይበር የትዊተር የውይይት ክበብ
የካቲት ፳፻፲፮ ዓ. ም

የኅልውና አደጋ ሲባል፤ ሆን ተብሎ ትርክት ተፈብርኮለት፣ አቀንቃኝ እና ደጋፊ ጀሌ ተፈጥሮለት፤ ሥርዓትም ተመሥርቶለት ዐማራውን በአካል፣ በኤኮኖሚ፣ በዕሴት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በአሰፋፈር፣ በቅስም፣ እንዲሁም የሱ በሆኑ እና ባልተዘረዘሩ ነገሮች ማዳከም እና ቢቻል ዝርው አድርጎ መበተንን እና ማጥፋትን ያለመ የተቀናጀ ጥቃት ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። በሌላ አገላለጽ፤ የዐማራ ሕዝብ የቆመባቸውን አዕማድ አንድ በአንድ ማፍረስ ወይም ማዳከም ተብሎ መገለጽ ይችላል። አሁን በደረስንበት ደረጃ፤ ዐማራን እና ዐማራነትን ከምድረ ገጽ የማጥፋት እሳቤ ግዘፈ አካል ነስቶ መንግሥታዊ ሥርዓት ከሆነ ሰነባብቷል፤ ክልል ተብሎ ከተሰጠውም ግዛት ገብቶ ጅምላ ፍጅት እያካሄደ ይገኛል። በሚከተሉት አንቀጾች፤ የኅልውና አደጋን መልከ ብዙ አመጣጦች ለማመልከት እንሞክራለን።

  1. ቀጥተኛ ፍጅት እና የዘር ማጥፋት፤
ቀጥተኛ ፍጅት እና የዘር ማጥፋት አንዱ እና በመጀመሪያ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል የኅልውና አደጋ ነው። ይህም በጅምላ ግድያ፣ ደብዛ በማጥፋት  እና ለተለያዩ የማይፈወሱ የአካል ጉዳቶች የሚዳርጉ ቀጥተኛ ጥቃቶች የመፈጸም ሥርዓት ተበጅቶለት ማኅበረሰብን በማጥቃት የሚካሄድ ሲሆን፤ በተራዘመ ሂደት ማኅበረሰቡን የማጥፋት አደጋ ነው።

  1. የማንነት ስሜት መደብዘዝ፤

ከተጎራባች ማኅበረሰቦች በበዛ ደረጃ የማንነት ስሜት መደብዝ ሌላኛው የኅልውና አደጋ ነው። በተለይ፤ የመንግሥታዊ ሥርዓቱ ሚእርሰው ጣልቃ ገብነት የራስን ማንነት በማኮሰስ በቋንቋ፣ በባህል፣ በኃይማኖት በሌሎች መገለጫዎች የራስን ጥሎ የተወናበደ ማንነት እንዲይዝ መደረጉ ለዘላቂ ኅልውናው አደጋ ሆኗል። የማንነት መደብዘዝ ክፋቱ፤ ከሌሎች የሚመጡ ጥቃቶችን በማንነት ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ለመረዳት፣ ብሎም ተሰባስቦ ለመከላከል ሊኖር የሚችል አቅምን ያመክናል። እንደምሳሌ፤ ዐማራው እንደ ዐማራ መጠቃት ከጀመረ፤ በርካታ አሥርት ዓመታት የሆኑት ቢሆንም፤ ይህንን በአግባቡ ለመረዳት ረጂም ጊዜ ወስዶበታል። የማንነት ጥቃቱም በኢትዮጵያውያን መካከል የተደረገ ተራ የጥቅም ግጭት እንዲመስል በማድረግ በዐማራዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንደ ዐማራ ተሰባስቦ መከላከል እንዳይቻል እንቅፋት ሆኗል። በተጨማሪም፤ አሁን እየተካሄደ በሚገኘው ዘርን የማስቀጠል ተጋድሎ፤ ዐማራዎች ሆነው ወንድም እህቶቻቸውን የሚገድሉ እና የሚያስገድሉ፤ አልፈውም ገዳዮቻቸውን የሚሸልሙ እና የሚያወድሱ ዐማራዎች መገኘታቸው ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት እንደሚሆን መበየን ይቻላል።
  1. የዐማራ ሕዝብ ታሪካዊ ሚና እና መዘዙ፤

የዐማራ ሕዝብ በዓለም ዙሪያ በነበሩ ግፉዓን ሕዝቦች የነጻነት ትግል ላይ የነበረውን ታሪካዊ የአርዓያነት ሚና በቅጡ አለማወቅ፣ ይህንን ተከትሎ የተነዙ ፀረ ዐማራ ትርክቶችን፣ የኃይል አሰላለፎችን እና ለኅልውና አደጋ ያጋለጡትን ሂደቶች ዘርዝሮ ባለመረዳቱ እና ራሱን ለመጠበቅ ባለመዘጋጀቱ ለኅልውና አደጋ ሊጋለጥ ችሏል።

  1. ከአጽመ ርስቶች መነቀል፤

ሌላኛው የዐማራ ሕዝብ የኅልውና አደጋ የሚመነጨው ከአጽመ ርስቶቹ በኃይል ከመነቀል ጋር የተያያዘ ነው። ይህ መፈናቀል በተለያዩ ዘመናት የተካሄደ ሲሆን፤  የዐማራ ሕዝብ ለደረሱ መፈናቀሎች ፍትሕ ሳይሰፍን ለተጨማሪ መፈናቀሎች እየተዳረገ ከዚህ ደርሷል። ይህም በተራዘመ ጊዜ በተካሄደ የቤተሰቦች መበተን፣ የትውልዶች መባዘን እና በመጨረሻም ባክኖ መቅረትን፤ ብሎም የማንነት መዋጥ እና የዘር መጥፋትን አስከትሏል። በቅርብ ዓመታትም በከተሞች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እና በማንነታቸው ዐማራ የሆኑ እንዲሁም የዐማራ ስነ ልቡና ያላቸው ሆኖም ዐማራ ያልሆኑ ዜጎች ፍትሕ አልባ መፈናቀሎች የዚሁ ሂደት አካል ናቸው። በውጤታቸውም ከላይ ከተጠቀሱት ተመሳሳይ ናቸው።

  1. በሂደት በኤኮኖሚ እንዲዳከም ማድረግ፤

በተዛባ የመሬት ይዞታ፣ የንግድ ሥርዓት፣ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት፣ ገቢን ያላገናዘበ ኢፍትሓዊ የግብር አጣጣል፣ የሸቀጥ ዝውውር እና የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት የዐማራ ሕዝብን የዕለት ተዕለት ሕይወትን በማመሰቃቀል ለተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች በመዳረግ በተራዘመ ሂደት ማጥፋት እየተሠራበት የቆየ የኅልዉና አደጋ ነው። ይህንን የሕይወት ምስቅልቅል ለመወጣት በሚደረጉ ትግሎች ወጣቶች እንዲሰደዱ በማድረግ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖራቸውና ትውልድ እንዳይተኩ በማድረግ፤ ለከፍተኛ የሞራል ውድቀት በመዳረግ፤ ከዚያም በስደተኝነት ሕይወት ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን የውጭ ምንዛሪ በመጠቀም ተጨማሪ ምስቅልቅሎችን መጥመቅ የምናየው ሐቅ ሆኗል። ይህም የትውልዶች ቅብብል እንዳይኖር በተራዘመ ሂደትም የማንነት መደብዘዝ፣ መጥፋት እና በመጨረሻም የዘር መጥፋት እንዲኖር አድርጓል።

  1. ስነ ሕይወታዊ የዘር ጥፋት፤

የዐማራ ሕዝብ ካለስምምነታቸው በቤተሰብ ምጣኔ እና በክትባት ሰበብ እንዲመክኑ ለዕድሜ ልክ ስነልቡናዊ ጉዳት እና ሕመም፤ እንዲሁም የሕዝብ ቁጥር እንዲዛባ፤ በዚያም ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር ሲሠራ መቆየቱን በማኅበራዊ ሚድያ ሲሰራጩ ከነበሩ ቃለ ምልልሶች ለመገንዘብ ችለናል። ይህ ለብዙ ዐማራዎች የአዕምሮ ከና አካላዊ ጤና፣ በምርታማነት እንዲሁም ለጤናማ ማኅበረሰብ ዕድገት እንቅፋት ከመሆን አልፎ ማኅበረሰቡን በተራዘመ ሂደት ለማጥፋት የተቀመረ ጥፋት እንደመሆኑ፤ ቀጥተኛ የኅልውና አደጋ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት፣ የበሽታዎች መከላከል፣ እንዲሁም የምግቦች እና የመድኃኒቶች ግብይት እና ቁጥጥር አገልግሎት ሆን ተብሎ እንዲዛባ በማድረግ የዐማራ ሕዝብን በጤና ማዳከም ሌላው የኅልዉና አደጋ ነው።

  1. ተጨማሪ ሥርዓታዊ ዘር የማጥፋት ሴራዎች፤

ከላይ ከተዘረዘሩት እና በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ሥርዓታዊ ሊባሉ ከሚችሉት ጥቃቶች በተጨማሪ፤ ይህ ክፍል በሕግ ሽፋን የሚደረጉ መልከ ብዙ ጥቃቶችን ያካትታል። ለምሳሌ፤ ፀረ ዐማራ ትርክቶችን በሕዝብ ገንዘብ ማስቀረጽ (ለምሳሌ፤ “የቡርቃ ዝምታ” እና ተከትሎም የ”አኖሌ ሐውልት”) እነዚህን እና የመሳስሉትን ለትውልድ እንዲዳረሱ ማድረግ (ለምሳሌ፤ በመማሪያ መጻሕፍት ከላይ የተጠቀሱትን ፀረ ዐማራ ትርክቶች ማስፈር እና ማስተማሪያ እንዲሆኑ ማድረግ፤ የራስ ደጀን ተራሮች እና የቅዱስ ላሊበላ አብያተ መቅደስ በትግራይ እንደሚገኙ ማስተማር እና የመሳስሉ)፣ በመንግሥታዊ ሚድያዎች የዐማራውን ባሕል ማጣጣል፣ የአማርኛ ስሞችን እየጠሩ መሳለቅ፣ በነዚህ ላይ ተመርኩዘው የተዘጋጁ “ዘፈኖች” እንዲሰራጩ ማድረግ፣ ዐማራ እንደዚህ ይላችኋል እየተባለ የተፈበረከ “ተረት ተረት” ማሰራጨት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የ”ዐማራ ዕምነት” ብሎ በመፈረጅ ማንጓጠጥ፣ ወዘተርፈ የተለመደ ሥርዓታዊ ተግባር ሆኖ ቆይቷል። በተጨማሪም፤ ዐማራዎች ዕድሜ ልካቸውን ቆጥበው የሠሩትን መጠለያ በማፍረስ እና ቤተሰባቸውን ካለምንም ጥሪት በመበተን የትውልዳቸውን ቀጣይነት እና ኅልውና አደጋ ላይ መጣል ሌላው የጥቃቱ መገለጫ ነው።

  1. ምሁራዊ ውርሶቹን እና ጸጋውን እንዳያዳብር እና እንዳይጠቀም የማድረግ ሴራዎች፤

የሰውን ልጆች ከሌሎች እንስሳት የሚለያቸው (ሌሎች አካላዊ ልዩነቶች ቢኖሩም) ዋናው ሊባል የሚችለው አዕምሮአዊ ጸጋው ነው። ይህም ከተለያዩ የአዕምሮ ክሂሎቶች መካከል፤ ምሁራዊ ክሂሎቶች የኅብረተሰቡን ምንነት፣ ማንነት፣ የኑሮ ፍልስፍና፣ የዕድገት ደረጃ፣ ሰላም/ ወይም የሰላም እጦት፣ ፍቅር/ወይም ጠብ፣ ባጠቃላይም እርስ በርሱ፣ ከተፈጥሮ እና ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር የሚኖረውን መስተጋብር የሚወስኑ እሳቤዎችን ማመንጨት እንደከፍተኛው ደረጃ ሊቆጠር ይችላል። ስለሆነም፤ የአንድ ማኅበረሰብ ኅልዉና በምሁራዊ ጸጋዎቹ እንደሚወስን ማሰብ ይቻላል።

የዐማራ ሕዝብ በታሪኩ ብዙ ምሁራን የነበሩት፣ አሁንም የበለጸጉ ጥንታዊ የዕውቀት ማዕከላት ያሉት፣ ልጆቹም ለትምህርት ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ የነበሩ እና እያደር በቁጥር እንዲያንሱ የማድረግ ጥረት ቢኖርም አሁንም ያሉ ናቸው። ሆኖም፤ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከተደረጉ አሻጥሮች መካከል፤ ሥርዓተ ትምህርቱ ከባህላዊው ልማድ እና ዕውቀት የተፋታ እንዲሆን ማድረግ፣ አድልዎአዊ የትምህርት ስርጭት ማድረግ፣ እየከፋ መጥቶም፤ ፊደላቱን ማጣጣል፣ ጥንታዊ ትምህርቶችን አስጥሎ በቅጂ ላይ የተመሠረቱ እና በራስ ወጭ ትውልዱን ለማደጎነት አሳልፈው የሰጡ የሕጻናት መዋያዎች እና ትምህርት ቤቶች መስፋፋታቸው፣ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል በአድልዎ እንዲሰጥ መደረጉ (ይህ እንደሀገርም ሲታይ ከፍተኛ የዕድል መነሳት ነው)፣ በየትምህርት ተቋማት የሚገኙ የዐማራ ተማሪዎች በተደጋጋሚ እንዲሳደዱ፣ እንዲሳቀቁ፣ እንዲሰወሩ፣ እንዲገደሉ፣ እንዲዋረዱ፣ በአጠቃላይም ተረጋግተው አንዳይማሩ መደረጉ፣ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አልፈው የሚመረቁ ተማሪዎች የሥራ ዕድል እንዳይኖራቸው የተለያዩ መሰናክሎች መደረጋቸው፣ ወጣቱ በሱስ እንዲጠመድ፣ ስነልቡናው በተለያዩ ሃይማኖት መሰል እንቅስቃሴዎች እንዲወናበድ መደረጉ፣ የተለያዩ አዕምሮ ማናወዣ የሚድያ ውጤቶች በማቅረብ እንዲደነዝዝ በማድረግ የወደፊት ዕጣ ፈንታ መንጠቅ፣ ወዘተርፈ አደገኛ የኅልውና አደጋ ነው።

  1. ቅርስ አልባ፣ ውርስ አልባ 'ማኅበረሰብ' የማድረግ ሴራዎች፤

እንደማንኛውም ማኅበረሰብ፤ የዐማራ ሕዝብ በስነ ሕንጻ፣ በስነ ቃል፣ በስነ ምግብ፣ በስነ ጽሑፍ፣ በስነ ጥበብ፣ በስነ ውበት፣ በግብርና፣ በማኅበረሰባዊ ተዋረድ፣ በኃይማኖታዊ ግብር እና መስተጋብር፣ በማኅበረሰባዊ ፍትሕ፣ በሥራ እና በዕረፍት አተገባበር፣ ከላይ ባልተካተቱ ባህላዊ ውርሶች፣ ወዘተርፈ ከትውልድ ወደትውልድ በቅብብሎሽ የተወረሱ እና እንደማኅበረሰቡ ዕድገት እየዳበሩ የሚመጡ ውርሶች ይኖሩታል። በተለይም ከላይ በተጠቀሰው የማንነት መደብዘዝ (ሰጥቶ በመቀበል ሊሆንም ላይሆንም በሚችል ሁኔታ)፤ አንዳንድ አዝጋሚ ለውጦች የሚጠበቁ ቢሆንም፤ በዋናነት በሥርዓተ ትምህርቱ፣  በሚድያ እና በቴክኖሎጂ ውጤቶች በሚመጡ አላስፈላጊ የሚድያ ስብከቶች እና መረጃዎች ምክንያት፤ በተጨማሪም በሹማምንት አቅም አልባነት እና በሙስና፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተሸረሸረ የመምጣት አደጋ ገጥሞታል።
ከሌሎች ባህሎች ጋር መማማር የማኅበረሰባዊ ዕድገት ዕውነታ መሆኑ ሳይዘነጋ፤ ሌላው ቀርቶ ተረት እና ምሳሌ ሞልቶ ፈሶ በነበረበት ባህል፤ ተረትና ጥቅስ ቅልውጥና ለመሄድ የተገደደ ትውልድ እንዲፈጠር ተደርጓል። ባህላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ከባህር ማዶ ተፈብርከው እንዲመጡ እና ገበያውን አንዲያጥለቀልቁት ሆኗል። በዚህም መጪው ትውልድ የአያት የቅድመ አያት ሙያውን ገዝቶ እንዲጠቀም፤ በልዋጩ ተቀጥሮ የመሥሪያ የሥራ ዕድል እንኳ እንዳያገኝ ተደርጓል። ይህ እንደ ኤኮኖሚያዊ ማድቀቅ፣ እንደ ማንነት ጥፋት፣ እንደ አዕምሮአዊ ጥፋት፣ ወይም ከነዚህ በሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑቱ የኅልውና አደጋዎች ጥምረት ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል።

  1. ማንነትን የለዩ ግፎችን እና በደሎችን መለማመድ፤

ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት፤ ምናልባት በውትድርና እና በዝቅተኛ መጠንም በሕክምና ሙያ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ይሆን ካልሆነ በስተቀር ለአማካዩ ዜጋ በአደጋም ይሁን ራስን በማጥፋት ወይም በዕድሜ/በበሽታ የሰው አስከሬን ማየት በጣም ዘግናኝ ክስተት እንደነበር እናስታውሳለን። ሆኖም፤ በተራዘመ ሂደት እየተፈጠረ ያለ የኅልዉና አደጋ፤ ከአንድም፣ አሥርቶች፣ ከአሥርቶችም መቶዎች፣ ከመቶዎችም ሺዎች (ቢያንስ በመርዶ መልክ) መስማት እየተለመደ  መምጣቱ ነው። ይህ ክስተት፤ ምናልባትም በተጠና መልክ የዐማራን ማኅበረሰብ በጅምላ የማደንዘዝ እና የጅምላ ስነልቡናዊ ቀውስ የመፍጠር ተልዕኮ እንዳለው በሚያስጠረጥር ደረጃ ቪድዮ እየተቀረጸ በማኅበራዊ ሚድያ እንዲሠራጭ እየተደረገ ይገኛል። የዚህ ተልዕኮ፤ አንድም፤ የዐማራ ሕይወት ያነሰ ዋጋ ያለው እንደሆነ በማኅበረሰቡ ስነ ልቡና ለመቅረጽ፤ ሁለትም፤ ተስፋ ለማስቆረጥ፤ ሶስትም ሁለንተናዊ የስብዕና ጥፋት ለማድረስ የሚደረግ የጅምላ ግፍ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህ ተግባር፤ ምናልባትም፤ ከላይ ከተዘረዘሩት የኅልዉና አደጋዎች በሁለተኛ ወይም በሶስተኛ ደረጃ ሊቀመጥ እንደሚችል ይገመታል።

Leave a Reply